ሕብረት ባንከ ከዘምዘም ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
ሕብረት ባንክ ከዘምዘም ባንክ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የቴክኒካል ትብብር የስምምነት ሰነድ ፊርማ በሕብረት ባንክ ዋና መ/ቤት ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈራረመ፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም ሁለቱ ባንኮች በቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርና ስልጠና አብረው የሚሰሩ ሲሆን ሕብረት ባንክም በዘርፉ ያለውን የካበተ እውቀትና ልምድ በማካፈል ለዘምዘም ባንክ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣል ፡፡
የስምምነት ሰነዱ በባንኮች መካከል ሲፈረም በአይነቱ የመጀመሪያ መሆኑን የገለፁት የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ ስምምነቱም በትብብርና በውድድር ውስጥ አብሮ መስራትን የሚያበረታታ፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀርና የውስጥ ሠራተኞችን አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ሕብረት ባንክ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን መስጠት ከጀመሩ ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ከሚሰጠው ዘምዘም ባንክ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ፊርማ በአቅም ግንባታ፣ የተለያዩ ተሞክሮዎችን በጋራ ለመጋራት እና ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡
የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው ስምምነቱ በባንኪንግ ኢንዱስትሪው ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልፀው የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረት እና የዕውቀት ሽግግርን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ባንኮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ሕብረት ባንክ
በሕብረት እንደግ!!