ሕብረት ባንክ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ35.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ::
ሕብረት ባንክ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ35.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ::
ሕብረት ባንክ. አ.ማ. ለአሥር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ የ35.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የሕብረት ባንክ የሸሪዓ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢብራሒም ዳውድ የተቸገሩትን መርዳት በአምላክ ዘንድ ሽልማትን የሚያስገኝ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ሕብረት ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሸሪዓው መርህ የተጣለበትን የግዴታ ሰደቃ በመወጣት ያደረገው ድጋፍ ቃልን በተግባር የመኖር ምሳሌ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሕብረት ባንክ ም/የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፋሲል አስናቀ በበኩላቸው ማሕበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እሴቱ የሆነው ሕብረት ባንክ ሸሪዓው በሚያዘውና በሰውም ሆነ በፈጣሪ ዘንድ መልካም በሆነው የማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ተግባር በማከናወኑ ክብር ይሰማዋል ብለዋል፡፡ አቶ ፋሲል አክለውም በማሕበረሰቡ ሕይወት ውስጥ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እና ማሕበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን መደገፍን ባንኩ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ባስተላለፉት መልዕክት የተቸገሩትን መርዳትና በጎ ሥራን መስራት ልብን የሚፈልግ መሆኑን እና ሕብረት ባንክም ለዚህ በጎ ተግባሩ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሕብረት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና የሸሪዓ ቦርድ አባላት፣ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ሕብረት ባንክ
በሕብረት እንደግ















