|

ሕብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ሕብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘ የአሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎትን ይፋ አደረገ

ሕብረት ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሕብር ኢ-ኮሜርስ የተሰኘና በኢትዮጵያ የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች በኦንላይን ለሸጡት እቃ ክፍያ በአለም አቀፍ የካርድ ክፍያ መንገዶች በውጭ ምንዛሬ መቀበል የሚያስችላቸውን የዲጂታል ፕላትፎርም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች፣ የሕብረት ባንክና የማስተር ካርድ የሥራ ኃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሕዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሕብረት ባንክ ዋናው መስርያ ቤት በይፋ አስተዋውቋል፡፡

በሕብር ኢኮሜርስ ይፋዊ የማብሰርያ ፕሮግራም ላይ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ሊድ የሆኑት ዶ/ር አብዮት ባዩ እንደተናገሩት በሀገራችን ያሉ አምራቾች ወደ ውጪ ምርቶቻቸውን ልከው ለሸጡትም ምርት በኦንላይን ፕላትፎርሞች በውጭ ምንዛሬ ክፍያ የሚያገኙበትን ስርዓት መዘርጋት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ በዛሬው እለትም ሕብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ያስጀመረው የሕብር ኢኮሜርስ መላ አምራቾችን በአለም አቀፍ መድረክ ተወዳደሪ የሚያደርጋቸውና ሀገራችንን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላት ነው፡

ብሔራዊ ባንክን በመወከል የተገኙት ወ/ሮ ማርታ ኃይለማርያም በበኩላቸው በሕብረት ባንክና በማስተር ካርድ መካከል የተደረገው የትብብር የስራ ስምምነት በሀገራችን የተለያዩ ምርቶችን አምርተው ወደ ውጪ ገበያ የሚልኩ ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀና የተቀላጠፈ የክፍያና ርክክብ ስርዓት ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው ብለዋል፡፡

የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ እንደተናገሩት የሕብር ኢ-ኮሜርስ ተግባራዊነት ከባንኩ ስትራቴጂ 2030 ጋር የሚጣጣምና በአለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ውስጥ በካርድ ባንኪንግ ለሚገበያየው ደንበኛ እና ለነጋዴው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ እንደገለፁት ሕብረት ባንክ የሞባይል ባንኪንግ ጨምሮ የተለያዩ የቴክኖሎጂ መላዎችን ለኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም መሆኑንና ለሚያስተዋውቃቸውም የቴክኖሎጂ መላዎች ደህንነትም የISO 27001:2013 ሰርተፊኬት ተሸላሚ በመሆን በሀገራችን የመጀመርያው ባንክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም ከማስተር ካርድ ጋር የተደረገው ትብብር የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ መሆኑን ገልፀው ይህ የኢኮሜርስ ክፍያ ስርዓት የሀገር ውስጥ ንግዶች በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁና እንዲስፋፉ የሚረዳ ነው፡፡

የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ካንትሪ ማኔጀር የሆኑት ሺኸርየር አሊ በበኩላቸው ‘’ይህ ትብብር ነጋዴዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የኦንላይን የክፍያ ጌትዌይ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውና ክፍያቸውን መቀበል፣ የደንበኞቻቸውን ቁጥርና ገቢያቸውን ማሳደግ የሚያስችላቸው ነው፡፡ ሺኸርየር አሊ አክለውም ይህ ስምምነት 50 ሚሊየን የሚጠጉ አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማትን ወደ ዲጅታል ኢኮኖሚው ለማስገባት የምናደርገዉን ጥረት የሚያግዝና ደህንነቱ የተጠበቀና ሁሉንም አገልግሎት አንድ ላይ ማግኘት የሚፈልጉ ተጠቃሚዎችን መድረስ የሚያስችል ነው፡፡ በዘርፉ በክፍያ ቴክኖሎጂ ቀዳሚ እንደመሆናችን ከሕብረት ባንክ ጋር በትብብር ያስተዋወቅነው የኢኮሜርስ ፕላትፎርም በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ምሕዳሩን የሚያሰፋና የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ አብረን በመስራታችን ኩራት ይሰማናል፡፡ ‘’ ብለዋል፡፡

Similar Posts