ሕብረት ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የገቢዎች ቢሮ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር የሦስትዮሽ የአገልግሎት አሰጣጥ ስምምነት ሠነድ ተፈራረመ፡፡
ሕብረት ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የገቢዎች ቢሮ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አሰባሰብ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችለውን የሦስትዮሽ የስምምነት ሠነድ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡
ይህ የስምምነት ፊርማ ‘ደራሽ’ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አሰባሰብ ፕላትፎርምን በመጠቀም ግብር ለመሰብሰብ የሚያስችልና ግብር ከፋዮች በባንኮች በኩል ክፍያቸውን በፕላትፎርሙ አማካኝነት ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው፡፡ ስምምነቱም ባንኮች ዘመናዊ የክፍያ ስርዓትን ከመተግበር ጋር ተያይዞ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ከማስቻሉም በላይ የደራሽ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ፕላትፎርም መፈጠር ለግብር አሰባሰብ ሂደቱ ቅልጥፍና እና ፍትሐዊነት አስተዋፅኦው አይነተኛ መሆኑን በስምምነት ፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ሕብረት ባንክን በመወከል የባንኩ ቺፍ ሪቴይል ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ ተሾመ ገብረ አብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የገቢዎች ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ተፈራ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን በመወከል ደግሞ የአስተዳደሩ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሀሚድ የስምምነት ሰነዱን ፈርመዋል፡፡
ሕብረት ባንክ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋርም በተመሳሳይ የደራሽ ፕላትፎርም ኤሌክትሮኒክስ ታክስ/E-TAX/ የግብር አሰባሰብ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ በጥቅም ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡
ሕብረት ባንክ
በሕብረት እንደግ!