ሕብረት ባንክ የተመሰረተበትን ሃያ አምስተኛ የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች
ያከብራል

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ-ሕዳር 11ቀን 2016 ዓ.ም.

በሀገራችን የግል ባንኮች ምስረታ ታሪክ ከቀዳሚዎቹ አንዱ የሆነውና በ1991 ዓ.ም ስራውን የጀመረው ሕብረት
ባንክ የተመሰረተበትን የሃያ ዓምስተኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በይፋ ማክበር መጀመሩን አስመልክቶ
በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው በሚቀጥሉት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ክብረ በዓሉን
የሚያከብር ሲሆን በዓሉንም አስመልክቶ በተቀመጡ መመዘኛዎች መሰረት ለተመረጡ አስር ግብረ-ሰናይ
ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ሕብረት ባንክ የሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ
የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ መላኩ ከበደ እንደተናገሩት ባለፉት ሃያ አምስት አመታት
ሕብረት ባንክ ያልተቋረጠ እድገት አስመዝገቧል፡፡ አቶ መላኩ አክለውም እንደገለፁት ሕብረት ባንክ በባንክ
ኢንደስትሪ ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በራስ አቅም በማዘመን ፈር-ቀዳጅ ሲሆን
አገልግሎቱንም ጊዜው በሚጠይቀው መልኩ እያሻሻለ እና እያዘመነ የመጣ የብዙዎች ተመራጭ ባንክ ነው፡፡

ባንኩ ሁሉንም አካታች የሆነ አሰራርን በመዘርጋትና የባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ብዙ ርቀት
መጓዙን አቶ መላኩ ገልፀዋል፡፡ አቶ መላኩ እንደተናገሩት ሕብረት ባንክ ያካበተውን ልምድና እውቀት ለሌሎች
በማካፈልም ረገድ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የነበረው ድርሻ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፣ በሕብረት እንደግ
የሚለውን መርሁን በተግባር ላይ በማዋልም የደንበኞችን ፍላጎት የሚመጥኑ አገልግሎቶችን በማቅረብና እንደ
አየር መንገድ፣ኢትዮ ቴሌኮም፣ሳፋሪኮም ኤም ፔሳ ካሉ ታዋቂ ድርጅቶች ጋር አጋርነት በመፍጠርም በቅንጅትና
በሕብረት ተመራጭ አገልግሎቶችን ለሕብረትሰቡ በማቅረብ ረገድም ተጠቃሽ ውጤት አስመዝግቧል፡፡

የሕብረት ባንክ ሃያ አምስተኛ አመት በዓል መከበር መጀመሩን አስመልክቶም የባንኩን የሃያ አምስት አመታት
ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽንም በይፋ ተከፍቷል፡፡ የፎቶ ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የባንኩ የዲሪክተሮች ቦርድ
ሰብሳቢ ኢንጂነር ሳምራዊት ጌታመሳይ ሲሆኑ በይፋዊ የመክፈቻ ፕሮግራሙ ወቅትም የሃያ አምስተኛው አመት
የብር ኢዮቤልዩ በዓል አከባበር መለያ ሎጎም ይፋ ተደርጓል፡፡

በሕብረት ባንክ ዋና መስርያ ቤት በተካሄደው የክብረ በዓሉ ይፋዊ ማስጀመርያ እና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ
የባንኩ የቦርድ አመራር አባላት፣ የባንኩ ማኔጅመንትና ሰራተኞች እንዲሁም የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ስለ ሕብረት ባንክ

ሕብረት ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው። ባንኩ ብዝሃነትን በሚያስከብርመሰረታዊ ዓላማ የተመሰረተ ባንክ ሲሆን መሥራች ባለአክሲዮኖቹ ባንኩን ለመመሥረት ሀብታቸውን በማጣመር በቁርጠኝነት ከተለያዩ የማሕበረሰባችን ክፍል የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ኢሜይል፡-info@hibretbank.com.et
ድረ ገፅ፡-www.hibretbank.com.et

Similar Posts