ሕብረት ባንክና ሰራተኞቹ የብር 5 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
በመቄዶንያ የሕብረት ባንክ ቀን ሆኖ በተሰየመው ጳጉሜን 4 ሕብረት ባንክና ሰራተኞቹ ለመቄዶንያ አረጋዊያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ መዕከል የ5,000,000 (አምስት ሚሊዮን) የብር ስጦታን አበረከቱ፡፡
በዕለቱም የሕብረት ባንክ የሥራ አመራር አባላት እንዲሁም የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች በማዕከሉ ተገኝተው ሕሙማኑንና በመገንባት ላይ የሚገኘዉን የማዕከሉን ሕንጻ በመጎብኘት አብሮነታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሕብረት ባንክ ተ/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ በማዕከሉ በመገኘት እንኳን ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ በሰላም አደራሳችሁ በማለት ስጦታውን ያበረከቱ ሲሆን ሕብረት ባንክ በራሱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የሕብረት ባንክ ሰራተኞችም ከደመወዛቸው በየወሩ በማዋጣት በቋሚነት የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማህበርን እየደገፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ አክለውም መቄዶንያ ለሁላችን ኩራት እንዲሁም ጧሪ ደጋፊ ለሌላቸው መጠለያ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ የሆነ በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ አብሮት ሊቆም የሚገባ ከመሆኑ ባሻገር በሀገራችን እንዲህ ያሉ ሥራዎች እንዲሰሩም ትልቅ ምሳሌ የሆነ ነው ብለዋል፡፡
የመቄዶንያ መስራች የሆኑት የክብር ዶ|ር ብንያም በለጠ በበኩላቸው ሕብረት ባንክና ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም ላደረጉት ድጋፍና አስተዋፅኦ እንዲሁም ለዛሬውና ለሁልጊዜ ለሚያደርጉት ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል፡፡
ባንኩ ለመቄዶንያ በተለያየ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን በመቄዶንያ የሕብረት ቀን ሆኖ በተሰየመው ጳጉሜን 4 በማዕከሉ በመገኘት ድጋፍ ሲያደርግ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ሕብረት ባንክ!
በሕብረት እንደግ!!